ታህሳስ ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት መልስ በርካታ አወዛጋቢ ነገሮችን ተናግረዋል።
በኤርትራ ዙሪያ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለምልልሳቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተተቹት አቶ ሀይለማርያም በዛሬው ንግግራቸው በተተቹበት ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረዋል። አቶ ሀይለማርያም ” አስመራ እሄዳለሁ ያልኩት በየትኛውም ቦታ እንደራደራለን የሚለውን የመንግስት አቋም አጽንኦት ለመስጠት ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስመራ ድረስ በመሄድ ከኤርትራ ጋር ለመደራደር እንደሚፈልጉ ከገለጹ፣ ለእኛ ለተቃዋሚዎችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋጋር ቢሮውን ክፍት ያድርጉልን” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ሀይለማርያም በቅርቡ የተሾሙትን ሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሁለቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ህጋዊ ጠቅላይ ሚኒሰትሮች ሳይሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማእረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚሰሩ ናቸው በማለት አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ መኖሩን እሳቸውም አቶ ደመቀ መኮንን መሆናቸውን ተናግረዋል።
አቶ ሀይለማርያም አንድ ም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ መኖሩን መናገራቸው በህወሀት እና በኦህዴድ ውስጥ ቀደም ብሎ የነበረው ስሜት ተመልሶ ሊፈጠር እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
አቶ ሀይለማርያም በኢትዮጵያ የተፈጠረው የጤፍ እጥረት ጤፍ በልቶ የማያውቀው ህዝብ ጤፍ መብላት በመጀመሩ ነው ብለዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ የስኳር ዋጋ የተወደደው አርሶ አደሩ ስኳር መብላት በመጀመሩ ነው በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ እንደሌለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment