ጥር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ በትናንትናው እለት ያካሄደው ስብሰባ ውጥረት የተሞላበትና የመንግስት ግልጽ ጫና የታየበት መሆኑን የቤተክህነት ምንጮች ገልጸዋል::
መንግስትም አቡነ መርቆሪዎስ መንበራቸው ላይ ተመልሰው ማየት እንደማይፈልግ በአቶ አባይ ጸሀዬ በኩል ግልጽ አቋሙን ያንጸባረቀ በመሆኑ የዕርቁ ጉዳይ ፍጻሜ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል::
በውጭ የሚገኙ አባቶች በዛሬው እለት በሎስ አንጀለስ በጀመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ በትላንትናው እለት ከካናዳ ሎስአንጀለስ ገብተዋል::
ትላንት በአዲስ አበባ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ለተገኙት አባቶች አቶ አባይ ጸሀዬ በግልጽ እንዳስታወቁት አቡነ መርቆሪዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ ማለት መንግስቱ ሀይለማሪያም ይመለስ ከማለት ተለይቶ አይታይም ማለታቸው ተሰምቷል::
መንግስት አቡነ መርቆሪዎስ ቢመለሱ ግድ እንደሌለው ነገር ግን ፓትሪያርክ ሆነው ማየት እንደማይፈልግ አቶ አባይ ጸሀዬ አረጋግጠዋል::
ስለሆነም የ 6 ኛውን የፓትርያርክ ምርጫ ሂደት እንዲያፋጥኑ እንዳሳሰቧቸውም መረዳት ተችሏል::
አንዳንድ ከመንግስት ጋር የሚሰሩ ጳጳሳት በተለይም ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመለሱ ከሆነ እኛም አክሱም ላይ የራሳችን ሲኖዶስ እናቋቁማለን በማለት ቤተክርስቲያኒቱን በግልጽ በዘር መስመር ለማስቀመጥ ሀሳብ መሰንዘራቸውን የተገኘው ዜና ያብራራል::
ዕርቁን የሚደግፉና አቡነ መርቆሪዎስን በመንበር ማየት የሚፈልጉ ጳጳሳት ቁጥር እየጨመረ የመጣ ቢሆንም መንግስት አቋሙን በግልጽ ማስቀመጡን ተከትሎ የመንግስትን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ ስብሰባው እንዲጠናቀቅ እየተጠበቀ ነው::
No comments:
Post a Comment