ጥር ፫ (ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሙዚቃው ለማነቃቃትና ለመደገፍ በመጪው ቅዳሜ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያመራ ቢቢሲ ዘገበ።
ከአርቲስቱ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረገው ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ፤ ቴዲ አፍሮን፦ “የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ልጅ የሆነ ድንቅ የፖፕ ስታር ሙዚቀኛ” ብሎታል።
ቀደም ሲል ባለፈው የእስር ጊዜ እና በአዲሱ አልበሙ ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረገው አርቲስት ቴዲ አፍሮ ለሁለት ዓመታት ታስሮበት ስለነበረው ሰው በመኪና ገጭቶ የመግደል ክስ ለቀረበለት ጥያቄ፦ ክሱን ባያምንበትም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ከመቀበል ውጪ አማራጭ እንዳልነበረው ተናግሯል።
ጥቁር ሰው የተሰኘው አልበሙ በዋነኝነት ባነጣጠረበት መልእክት ዙሪያ ያብራራለት ዘንድ የቢቢሲው ዘጋቢ ላቀረበለት ተከታይ ጥያቄም፦” በአፄ ምኒልክ ብልህ አመራር ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አባቶች በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ አድዋ ላይ የተቀዳጁት ድል የ አፍሪካና የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል መሆኑን በማንጸባረቅ፤ ያን ታላቅ ድል የተቀዳጁትን ጀግኖች ማወደስ እንደሆነ አስረድቷል።
No comments:
Post a Comment