FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, December 21, 2012

“የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” የምሥረታ መግለጫና ሃገራዊ ጥሪ


GPF Pict 2
ቀን ታህሳስ 11 2005
የወያኔን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በትጥቅ ትግል ለማስወገድ “የግንቦት7 ሕዝባዊ ኃይል” የሚል ስያሜ የሰጠነውን፣ በሃገር ወዳድና ለህዝብ ተቆርቋሪ በሆኑ ወጣቶች፣ ምሁራንና ዜጎች የተሞላውን ድርጅት መመሥረታችን በዛሬው እለት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ እናበስራልን።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል፣ የሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባት፤ የዜጎች መብቶች፣ ሃገራዊ አንድነት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበሩባት ጠንካራና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ሆና የማየትን ራዕይ የሰነቀ ድርጅት ነው።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ወያኔን በኃይል የማስወገድ፤ ሰላማዊና ዲሞክራሲ የሥልጣን ሽግግር በሃገሪቱ እንዲኖር የማስቻል እና ከማንኛዉም የፓለቲካ ድርጅት ጋር ያልወገኑ ነፃ፣ ጠንካራና ብቃት ያላቸው ህገ-መንግሥታዊ የመከላከያ፣ የፓሊስና የደህንነት ተቋማት እንዲኖሩ አስተዋጽዖ የማድረግ ተልዕኮ ይዞ የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ ነው።
የግንቦት7 ሕዝባዊ ኃይል ራዕይና ተልዕኮ የተቀዳው በቀጥታ ሕዝብ በህይወቱ በደሙ በስቃይና በመከራ ውድ መስዋዕትነት ከከፈለለት የ1997 ብሄራዊ ምርጫ ነው።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይልን እውን ያደረገው ወያኔ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በስልጣን ለመቆየት በምርጫው ማግስትና እስካለንበት ወቅት በወሰደውና እየወሰደ ካለው የእብሪት እርምጃ ነው።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ወያኔ ድርድርና እርቅ የማይገባው፣ ትዕግስትን እንደፍራቻ፣ አርቆ አሳቢነት እንደ ሞኝነት የሚቆጥር በዚህም ስሌት ሕዝብን ለዘላላም እየረገጠና እየዘረፈ ለመግዛት ቆርጦ የተነሳ እኩይ ኃይል መሆኑ ጠንቅቆ የተረዳ ነው። የወያኔ አገዛዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተወለት ምርጫ በዝምታ በባርነት መገዛት ወይም ለነጻነት መዋጋትን ብቻ መሆኑን የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ጠንቅቆ ያውቃል ።
በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ውስጥ የተሰባሰብን ዜጎች በደማችን የሚፈስ የቀደምቶቻችንን የነጻነት ቅርስ ተሸካሚዎች ነንና ባርነትን አማራጭ አድርገን ለመቀበል ከቶውኑ አይቻለንም። ብቸኛው ምርጫ የወያኔን የባርነት ግብዣ በአመጽ መክተን በወያኔ መቃብር ላይ የነጻነትን ሰንደቅ ማውለብለብ ነው።
ዛሬ በሃገራችን በወያኔ አምባገነናዊ እብሪት ያልታፈነ፣ ያልተዋረደና ያልተዘረፈ የሃገሪቱ ዜጋ አይገኝም። የወያኔ ሹማምንት በሃብት ላይ ሃብት፤ በድሎት ላይ ድሎት ሲጨምሩ፣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እጣ ፈንታ ግን መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መንገላታት፣ መታሰር፣ መደብደብና መገደል ሆኗል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን እንደ ወያኔ ዘመን የተዋረዱበት፣ የተናቁበትና የተበደሉበት ጊዜ የለም። የዚህ ሁሉ ሰቆቃ አብይ ምክንያት የወያኔ ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ ነው። ወያኔ ከሥልጣን ሳይባረር አንዳችም በጎ ለውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብ አይቻልም።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የወያኔን እኩይ ባህሪያትና ተፈጥሮ በመመርመር፣ የወያኔ የአመጽ እብሪት በሕዝባዊ አመጽ የሚተነፍስበት ሁኔታ እስካልመጣ ድረስ፣ ወያኔ መብታቸውን ከመጠየቅ ውጭ ምንም እንከን የሌለባቸውን ንጹሃን ዜጎች ከማሰር፣ ሰቆቃ ከመፈጸም፣ ከመግደል ከማሳደድና ከማፈናቀል እንደማይቦዝን ከልብ ያምናል።
ሁላችንም ሃገራችንን ነጻነታችንን የምንወድ ዜጎች ያለን ምርጫ ቀበቷችንንና መቀነታችንን ጠበቅ፣ ሃሞታችንን ኮስተር አድርገን ወያኔ ያሳጣንን ሰላምና ነጻነት፡ የቀማንን ሃገርና አንድነት በመራራው ትግላችን ማስመለስ ብቻ ነው።
የግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል በዛሬው እለት ራሱን ይፋ ያደረገው ይህ ወያኔን የማስወገድ ትግል የተጀመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀውና ትግሉን እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪውን ለማሰማት ነው ።
ህገ- መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሰላማዊ ተቃውሞዎች ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ዜጎች በሽብርተኛነት እየተከሰሱ በእድሜ ልክ እስራት ሲቀጡና ሰቆቃ ሲፈፀምባቸው የታዘባችሁ ወጣቶች፤
ለሃይማኖት እኩልነት በመታገላቸው በእስር ላይ እየማቀቁ፣ እየተገረፉና እየተሰቃዩ ያሉ የሙስሊም ምዕመናን ተወካዮች ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ወገኖች፤
በቤተክህነትና በክርስትና ተቋማት ላይ እየተፈፀመ ያለው ደባ የሚያንገበግባችሁ ወገኖች ሁሉ፤
ለወያኔዎችና ሸሪኮቻቸው እድገትና ምቾት ሲባል ከይዞታችሁ የተፈናቀላችሁ ወገኖቻችን ሁሉ፤
በወያኔ ቱጃሮች ሥራችሁ መቀማቱ ሳያንስ፣ ገቢን ሳይሆን ወገንተኛነትን መስፈረት ባደረገ መመዘኛ ከአቅም በላይ የሆነ የወያኔ ግብር፣ ታክስና መዋጮ የተማረራችሁ ነጋዴዎች፤
ማኅበራችሁ በወያኔ ፈርሶ ወይም ተጠልፎ የጋራ ድምፃችሁን የምታሰሙበት፣ ከቀጣሪያችሁ ከወያኔ ጋር ፍትሃዊ የጉልበታችሁን ዋጋ ክፍያ መደራደሪያ ያጣችሁ ላብአደሮች፣ መምህራን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች፤
ምንም አይነት የአካዳሚ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ጥራቱን ያልጠበቀ ትምህርት እንድትከታተሉ የተፈረደባችሁ፣ ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ከየኮሌጁና ከየዩንቨርስቲው ስትመረቁ እጣችሁ ድንጋይ ማንጠፍ የሆነው ወጣት ተማሪዎች ፣
በነጻነት ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ ለመኖር የተሳናችሁ፣ በገዛ ሃገራችሁ ገና በጎልማሳ እድሜችሁ የወላጆቻችሁ ጡረተኞች እንድትሆኑ የተፈረደባችሁ፣ እንደ ወላጆቻችሁ ትዳር መስርታችሁ ልጆች ወልዳችሁ የመሳም እድላችሁ በወያኔ ዘረኛና ዘራፊ ፖሊሲዎች ጨንግፎ የቀረባችሁ፣ አደገኛ በረሃዎችንና ባህሮችን በማቋረጥ ለመሰደድ ልባችሁ እየከጀለ ያለ የሃገራችን ውድ ወጣቶች፤
በአረብ ሃገራት ለባርነት ስራ በወያኔ እየተሸጣችሁ፣ እጣችሁ ተገዶ መደፈር፣ በፈላው ወሃ መቀቀል፣ መደብደብ፣ መዋረድና ከፎቅ ላይ እየተወረሩ ክቡር ህይወትን ማጣት ለሆነው ውድ እህቶች፣
ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ግድ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በሙሉ፤
የሕዝብ ድምጽ ይከበር በማለታችሁ፣ ለሃገር አንድነትና ክብር መሰለፍ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባችሁ እንደ ባዕድ ጦር የተበተናችሁና የተገፋችሁ፣ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በሚታየው ዘረኛነት እየተቃጠላችሁ፣ በሕዝብ ላይ ዝመቱ በተባላችሁ ቁጥር ከህሊናችሁ ጋር መዳማት የመረራችሁ የኢትዮጵያ ወታደሮች እና፤
በድህነት አስገዳጅነት፣ እንዲሁም በሌሎችም ማስፈራሪያዎችና ጫናዎች የወያኔ/ኢህአዴግ ድርጅቶች አባል የሆናችሁ ወገኖቻችን በሙሉ፣
ዛሬ ነገ ሳትሉ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይላችንን ተቀላቀሉ።
ተባብረን ወያኔን እናስወግድ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
አድራሻ: ስልክ ቁጥር – +442081230056
ኢሜል አድራሻ pr@ginbot7pf.org

No comments:

Post a Comment